July 21, 2026
ተደራሽ ማህበረሰብ አቀፍ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ሥራ ማህበር በአገር አቀፍ ደረጃ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 33 በማድረስ እና ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ካፒታል በማፍራት የ9ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በዛሬው ዕለት በድምቀት አክብሯል። በ4 ኪሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፖስታ ህንፃ ዋና ቢሮ በተካሄደው በዚህ ስነ-ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጌትነት ታደሰ፣ ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ ሙመድ፣ የተቋሙ የሥራ አመራር ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አልማዝ ኦልጅራን ጨምሮ የክልልና የከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የማህበሩ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ታመነ እንደገለፁት፣ ተቋሙ በሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም በ24 መስራች አባላት እና በ24 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ የተመሰረተ ሲሆን፣ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት በቤተሰብ ደረጃ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም ከመስከረም 2013 ዓ.ም ጀምሮ ባደረገው አዲስ የአሠራር ለውጥና ባለፉት ስድስት ዓመታት ባካሄደው ስትራቴጂካዊ የሪፎርም ንቅናቄ አሁን ላይ የአባላቱን ቁጥር ከ27 ሺህ 900 በላይ ማድረስ ችሏል።
እስካሁን ባለው ጉዞው ከ2,500 በላይ አባላትን የብድር ተጠቃሚ ያደረገው ተደራሽ፤ 443 አባላትን የቤት ባለቤት፣ 452 አባላትን ደግሞ የሥራና የቤት መኪና እንዲሁም የባጃጅ ባለቤት ማድረግ የቻለ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከ13 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ወደፊትም በቀጣይ 17 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 50 ለማድረስ ያቀደ ሲሆን፣ የዲጂታል ኮር ባንኪንግ ሥርዓቱን ይበልጥ በማጠናከር የአገሪቱን ማዕከላዊ የፋይናንስ ክምችት ለማሳደግ የድርሻውን እያበረከተ፣ እ.ኤ.አ በ2029 ከአፍሪካ ምርጥ 10 የቁጠባና ብድር ተቋማት ተርታ ለመሰለፍ ትልቅ ራዕይ ሰንቆ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።